Monday, 19 March 2018

ክቡር ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ 122ኛው የዓድዋ ድል በዓለን በዓድዋ አከበሩ

የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም
በኢትዮጵያዊያን መካከል ምንም አይነት ልዩነት ቢኖርም የሀገር ጉዳይ ሲነሳ ልዩነታቸውን ወደጎን ትተው የጋራ ለሆነው አጀንዳ ቅድሚያ እንደሚሰጡ የዓድዋው ጦርነት አብይ ማሳያ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ፡፡


ክቡር ፕሬዝደንቱ 122ኛውየዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን ድሉ በተበሰረበት የሰሎዳ ተራራ ስር በአካል ተገኝተው አክብረዋል፤ በዓሉን አስመልክተውም ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም የዓድዋ ድል መሰረታዊ ሚስጥር ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ካላቸው ቀናዒነት የተነሳ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በአንድነት መነሳት መቻላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ 

ቅኝ ገዢዎች መላው አፍሪካን ለመቀራመት የሚስችላቸውን የበርሊን ኮንፈረንስ ካካሄዱ ከ11 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ለመውረር ገስግሶ የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ኃይል በዓድዋ ድል በመመታቱ ምኞቱ መና ሆኖ መቅረቱን አክለው ገልፀዋል ክቡር ፕሬዝደንቱ፡፡ 

“የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ያሳየ፤ መላው ጥቁር ህዝቦችን ለነፃነት ትግል ያነሳሳ፤ ጦርነትን ድል የማድረግ መሰረታዊ መነሻ የመሳሪያ ሃይል ሳይሆን ፍትህ መሆኑን ያሳየ ነው” ብለዋል ክቡር ፕሬዝደንቱ፡፡

ክቡር ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙላቱ በ122ኛው የዓድዋ ድልን በቦታው ተገኝተው ከማክበር ባለፈ የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ኦህዴድ የተመሰረተበትን የናዕዴር ኣዴት ወረዳን አንዳንድ ቦታዎችን በተለይም ምስረታው እውን የሆነበትን ዋሻ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment